ማንዴላ በነገው እለት በሚካሄድ ትልቅ ዝግጅት ታስበው ይውላሉ

– ዝግጅቱ በአፍሪካ ትልቁ የመሪዎች ስብስብ የሚያስተናግድ ስነ-ስርዓት ይሆናል ተብሎአል
– ባራክ ኦባማ እና ሶስት የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚደንቶች፣ ዝነኛዋ ኦፕራ ዊንፍሬይ ይታደማሉ

mandela

በተወለዱ በ95 አመታቸው ባለፈው ሃሙስ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የደቡባ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደን እና የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኝ 90ሺ ሰው በሚይዝ ስቴድየም ታስበው ይውላሉ። 91 የአገር መሪዎች በእለቱ እንደሚገኙ የተረጋገጠ ሲሆን በተጨማሪ በርካታ የቀድሞ መሪዎች፣ የነጻነት ታጋዮች፣ ታዋቂ ሰዎች እና የሃይማኖት አባቶች በስፍራው ይታደማሉ። በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የመሪዎች ስብስብ እንደሚሆን የተነገረለት ይህ ስነ ስርዓት በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በስቴድየሙ አቅራቢያ እንደሚታደሙ ተጠብቋል።

በማንዴላ ሞት በርካታ ሃገሮች የሃዘን ቀን በማወጅ ለማንዴላ ያላቸውን አድናቆት የገለጹ ሲሆን ብዙዎች የማንዴላን ንግግሮች፣ ታሪካቸውን እና ጽሁፎቻቸውን በድጋሚ በማስታወስ ማንዴላን አወድሰዋል። ታዋቂው ድህረ ገጽ ዩቲዩብ የማንዴላ ቪዲዮዎች ተመልካች በ400 እጥፍ የጨመረ ሲሆን ትዊተርም በሁለት ሰዓት ውስጥ 72 ሚሊዮን ማንዴላን የተመለከቱ መልክቶች ተሰራጭተውበታል።

የማንዴላ አጭር የህይወት ታሪክ

በዕለተ ሐምሌ 11፣ 1910 ትራንስኪ በሚባል አካባቢ በምትገኝ ምቬዞ በተባለች መንደር ከአባታቸው ሀነርይ ምጋድላ ማንዴላ እና እናታቸው ኖንኳፊ ኖሴኬኒ የተወለዱት ሮሂላህላ ማንዴላ በካባቢያቸው በሚገኝ ሚሲዮናዊ ትምህርት ቤት መማር ሲጀምሩ ነበር አስተማሪያቸው ኔልሰን የሚለውን ስም የሰጧቸው። አባታቸው በአካባቢው አስተዳዳር ውስጥ ተሳታፊ ስለነበሩ ወደፊት አመራር እንደሚሆን ተጠብቆ የነበሩት ማንዴላ አባታቸው ከዚህ አለም በሞት ከተለየ በኋላ ከአካባቢው ገዢ ቤት በመኖር ባህላዊ የአመራር እና የአስተዳደር ጥበቦችን ይቀስሙ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በቤተዘመድ የመጣለትን ጋብቻ ባለመቀበል ከቤት ጠፍቶ ወደ ጆሃንስበርግ በመምጣት ከአፓርታይድ ስርዓት ጋር ተዋወቀ።

ከዛም ዩንቨርስቲ በመግባት የህግ ትምህርቱን እየተከታተለ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ(አብኮ) በመቀላቀል ፖለቲካን በ1935ዓ.ም ሀ ብሎ ጀመረ። ጥቁር ህዝቦች በትምህርት እንዲገፉ በማይበረታታበት የአፓርታይድ ስርዓት ውስጥ የህግ ማማከር ድርጅት ውስጥ በመቀጠር ወገኖቹን መርዳት የጀመረው ማንዴላ የመጀመሪያ ባለቤቱ እቨሊን ሜስ ጋር ተዋውቆ ትዳር መስርቶ ነበር። ከመጀመሪያ ትዳሩ አራት ልጆች ያፈራ ሲሆን ትዳሩ መቀጠል ሳይችል በ1947 ተለያይተው 1950ዓ.ም በፍቺ ተጠናቀቀ።

ፖለቲካን የጀመረበት አብኮ ወጣቶችን ወደ ድርጅቱ በማምጣት ህዝቡን በፀረ አፓርታይድ ትግሉ ለማሳተፍ በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ከታዋቂዎቹ ታጋዮች ኦሊቨር ታምቦ፣ ዋልተር ሲሱሉ እና ሌሎችም ጋር በመሆን ትልቅ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ። በ1944 ዓ.ም ይህ የወጣቶች ስብስብ ህዝባዊ አልታዘዝ ባይነት እና አድማን እንደ ትግል ስልት በመያዝ አፓርታይድ ስርዓትን ለማዳከም የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከፊት በመሆን ይመራ ስለነበር በወንጀል ተከሶ በአነስተኛ ቅጣት ታለፈ። በዚያው አመት ማንዴላ የመጀመሪያውን የጥቁር የህግ ማማከሪያ ድርጅት በመክፈት በብዛት ህግ ፊት ካለ በቂ ጠበቃ ለሚንገላቱ ጥቁሮች መቆም ጀመረ። ይህ ያልተዋጠለት የአፓርታይድ አገዛዝ ቢሮውን ከከተማ ውጪ እንዲያወጣ በማዘዝ ደንበኞቹ በቀላሉ እንዳያገኙት ሆኗል።

የአፓርታይድ ስርዓት የሱን በፖለቲካው ተሳትፎ ማድረግ ስላልፈቀደ በ1945 ለሁለት አመት ቀጥሎም በ1947 ለአምስት አመት እገዳ ከመጣል አልፈው እገዳው ገና ሳያልቅ ማንዴላ እና ጓዶቹ ሃገር በመክዳት ክስ ተከሰው ፍርድ ቤት በመመላለስ ላይ ነበር ከሁለተኛ ሚቱ ዊኒ ማንዴላ ጋር በ1950 ትዳር የመሰረተው። ከሁለተኛ ሚስቱ ማንዴላ ሁለት ልጆችን አፍርቷል። በ1953 በደቡብ አፍሪካ በተከሰተ የመንግስት ለውጥ ክሱ ቢቋረጥም የጥቁሮች መገለል የሚደግፉ ህጎች መኖራቸውን በመንቀፍ ማንዴላ ትግሉ ለማጠንከር አለም አቀፍ እንቅስቃሴ ማድረግ ቀጠለ። ይህንን ለማስተባበር ደቡብ አፍሪካን በመልቀቅ የተለያዩ አፍሪካ ሃገራት እና እንግሊዝን ከጎበኘ በኋላ ወደ ኢትዮጲያ በመሄድ የወታደራዊ እና አስተዳደር ትምህርት ከተከታተለ በኋላ በ1955 ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደተመለሰ በቁጥጥር ስር ውሎ አገር በመክዳት እና መንግስት ለመገልበጥ በመሞከር እና በሽብር ወንጀል ተከሶ እድሜ ልክ ተፈረደበት። ቤተሰብም ኦነ ደጋፊዎቹ እንዳይጠይቁት ለማድረግ ውሃ መሃል በሚገኝ የደሴት እስር ቤት የታሰረው ማንዴላ ድንጋይ በእስር ቤት ጠባቂዎቹ ከሚደርስበት በደል በተጨማሪ እንዲሰራ የተገደደው የድንጋይ መጥረብ ስራ በሚፈጥረው የፀሃይ ጨረር አይኑ ተጎድቶ ነበር።

በ1974 ኬፕ ታውን ወደሚገኝ እስር ቤት ከተላለፈ ከሶስት አመት በኋላ የአፓርታይድን ስርዓት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ውይይት ማድረግ ጀመረ። አፓርታይድ ስርዓቱ የሱ የትውልድ አካባቢ ነጻ አገር እንዲሆኑ በመፍቀድ እና እሱን ወደዛ ሄዶ ነጻ ሰው እንዲሆን ቢጠይቁትም እሱ ስለመላው ደቡብ አፍሪካ እንደሚታገል በመግለጽ ውድቅ ያደረገ ሲሆን በተጨማሪም “ድርድር ማድረግ የሚችለው ነጻ ሰው ስለሆነ እስረኛ ሆኜ አልደራደርም” በማለት ጥያቄዎችን ሲገፋ ነበር። በመጨረሻ በ1981 የተመቸ እስር ቤት ተዛውሮ ድርድሩን በመቀጠል ከታሰረ ከ27 ዓመት በኋላ በ1982 ከእስር ሊፈታ ችሎአል። ከነጻነት በኋላ ወደ ኢትዮጲያ በመምጣት የህክምና አገልግሎት ካገኘ በኋላ ሌሎች አገራትን ጎብኝቶ ወደ አገሩ በመመለስ ዘረኛውን ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ለማጥፋት የሚደረገውን የመጨረሻ ጉዞ በሰከነ አመራር ማስቀጠል ቻለ።

ህገወጥ የነበረው አብኮ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ከአመት በኋላ ትልቅ ጉባኤ ያደረገ ሲሆን ከዛም ከሶስት አመታት በኋላ በ1986 በሃገሪቱ በተካሄደ ሁሉን አሳታፊ ምርጫ የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ጥቁር መሪ በመሆን ስልጣን ያዘ። በወቅቱ ለግጭት እና ጥፋት አፋፍ ላይ የነበረችውን አገር ይቅር መባባል እና መተማመን ላይ መሰረት ባደረገ ስልት የነጩን ስርዓት ጥፋት ሳይረሳ ነገር ግን በይቅርታ በማለፍ የተረጋጋ አመራር መመስረት ችሎአል። በ1988 ከሁለተኛ ባለቤቱ ጋር ከተፋታ በኋላ በ1990 ሞዛምቢካዊቷ ሶስተኛ ባለቤቱ ግራሺአ ሚሼል ጋር ትዳር መሰረተ። ለ5 አመት አገሪቷን ከመራ በኋላ ቀጣዩ ትውልድ መረከብ አለበት በሚል አስተሳሰብ በድጋሚ ፕሬዜደንት ለመሆን እንደማይወዳደር እና “የቅርብ ተመልካች የሩቅ ተቺ” እንደሚሆን በመግለጽ ከፖለቲካው መራቅ ጀመረ። በሱ የአመራር ግዜ በአለም አቀፍ ማዕቀብ ተዳክሞ የነበረው ኢኮኖሚ ማገገም የጀመረ ሲሆን ጥቁር ህዝቦችም ነጻነታቸው ተከብሮ ከነጮች እኩል መብት አግኝተው ነበር። በማንዴላ ሰፊ ተሳትፎ ደቡብ አፍሪካ በአሃጉሩ የመጀመሪያ የሆነው የአለም ዋንጫ ማዘጋጀት ችላለች።

ማንዴላ ከፖለቲካ ከተገለሉ በኋላ ሶስት ፋውንዴሽኖችን በማቋቋም የበጎ ስራ አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን በሽታ እስኪያስቸግራቸው ግዜ ድረስ ከከተማ በመውጣት የትውልድ መንደራቸው ውስጥ መኖር ጀምረው ነበር። በእስር ቤት በነበሩበት ወቅት የያዛቸው የሳንብ በሽታ በእድሜአቸው መጨረሻ በርትቶ ወደ ሆስፒታል መመላለስ አብዝተው በመጨረሻ ህዳር 26፣ 2006 ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ማንዴላ በታዋቂው ሃርቫርድ ዩንቨርስቲ ያደረጉትን ንግግር ከስር ይመልከቱ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s