ሌስተር ሲቲ የ2015/16 እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አነሳ

ሌስተር ሲቲ የ2015/16 እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አነሳ

ሌስተር ሲቲ የ2015/16 እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አነሳ

በኪንግ ፓወር ስታድየማቸው ዛሬ ከኤቨርተርን ጋር የተጫወተው ሌስተር ሲቲ የዘንድሮውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አነሳ። ሌስተርን ሻምፒዮናነቱን ያረጋገጠው በሁለተኛነት ይከተል የነበረው ቶትንሃም ባለፈው ሰኞ ማታ ከቼልሲ ጋር ባደረገው ጨዋታ ሁለት አቻ ከተለያየ በኋላ ነበር። ከሁለት አመት በፊት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ሌስተር ዘንድሮ ዋንጫ የመብላት እድሉ በአወራራጆች 5000/1 እድል የተሰጠው ቢሆንም ባልተጠበቀ ሁኔታ አሸናፊ ሆኖ አስገራሚ ታሪክ ጽፏል።

ሌስተር በ132 ዓመት ታሪኩ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮና ሲሆን የመጀመርያው ሲሆን ድላቸውን ጣፋጭ ያረገው ደግሞ ትንሽ ቡድን ሆኖ ብዙ ገንዘብ የሚያወጡትን እነ ማንቸስተር ሲቲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቼልሲን የሚያክሉ ትልቅ ቡድኖችን አስከትሎ ሻምፒዮን መሆኑ ነው። በውድድሩ ዘመን መጀመሪያ ወደ ቡድኑ የመጡት ታዋቂው ጣልያናዊ አሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኒየሪም በድሉ የመጀመሪያቸው የሆነውን የሻምፒዮን ዋንጫ ከሌስተር ጋር አንስተዋል። ቡድኑ ታዋቂ ያልነበሩ እና ብዙ ገነዘብ ያልወጣባቸው ተጫዋቾች ይዞ ቢጀምርም ወደ ሻምፒዮና በሚያደርጉት ጉዞ ዴንማርካዊው ጎል ጠባቂያቸው ካስፐር ሺማይክል፣ እንግሊዛዊው ኮከብ ጎል አግቢያቸው ጄሚ ቫርዲ፣ አማካዮቻቸው አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ፣ ፈረንሳዊው ንጎሎ ካንቴ እና እንግሊዛዊው ዳኒ ድሪንክዋተር ጎልተው በመውጣት ትላልቅ ክለቦች አይን ውስጥ እንዲሁም ብሄራዊ ቡድኖቻቸው ውስጥ መግባት ችለዋል።

ሌስተሮች በኳስ ቁጥጥር እና በማራኪ ጨዋታ ጎልተው ባይወጡም በጥሩ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት ጨዋታቸው የተዋጣላቸው ነበሩ። ከሁሉም በላይ በውድድር ዘመኑ መለያቸው የነበረው የነበራቸው የቡድን ስሜት እና መደጋገፍ ነበር። ሌስተር በመጪው አመት በታላቁ የአውሮያ ቻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፍ ሲሆን አሰልጣኝ ራኒየሪ የቀጣዩ አመት ፕሪሚየር ሊግ አላማቸው እስከ አስረኛ ለመጨረስ እንደሆነ ተናግረዋል።

Advertisements

ሊዮኔል ሜሲን ሎጬ ማስገባት የሚስተካከለው የለም

እግር ኳስ ጨዋታ ላይ ኳሷን በተጋጣሚ ተጫዋች እግሮች መሃል ማሳለፍ (ሎጬ ማስገባት) የአርጀንቲናውን ተዓምረኛ ሊዮኔል ሜሲን የሚስተካከለው የለም

የዘንድሮውን አለም ዋንጫ ለማሸነፍ የሚችል ብቃት ያለው የአውሮፓ ቡድን ኔዘርላንድ ነው

የኔዘርላንድ ቡድን

የኔዘርላንድ ቡድን

ከአራት አመት በፊት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ግዜ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የአለም ዋንጫ ዘንድሮ ከከተመበት ብራዚል መካሄድ ከጀመረ ቀናት አስቆጥሮአል። በደቡብ አሜሪካ ሲካሄድ የዘንድሮው አለም ዋንጫ ለአምስተኛ ግዜ ሲሆን ብራዚል ውድድሩን አሁን ስታዘጋጅ ለሁለተኛ ግዜ ነው። ለመጀመሪያ ግዜ ከሃምሳ አራት አመት በፊት በ1942 ብራዚአል ባዘጋጀችው አለም ዋንጫ ለፍጻሜ ከኡራጓይ ጋር ብትቀርብም በደጋፊዋ ፊት ተሸንፋ ኡራጓይ ዋንጫው እዛው ደቡብ አሜሪካ አስቀርታዋልች። በአጠቃላይ አለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ የሚታየው ሌላው ውድድር በአውሮፓ በተካሄደ ውድድር ስንት የደቡብ አሜሪካ ቡድን አሸነፈ ወይም ደቡብ አሜሪካ በተካሄደ ውድድር ስንት የአውሮፓ ቡድን አሸነፈ የሚል ፉክክር ይገኝበታል። በዚህ ፉክክር እስከዛሬ በአውሮፓ ከተደረጉ አስር የአለም ዋንጫ ውድድሮች ደቡብ አሜሪካ አንድ ግዜ ሲያሸንፍ በደቡብ አሜሪካ በተደረጉ አራት ውድድሮች እስካሁን ያሸነፈ የአውሮፓ አገር የለም። በሰሜን አሜሪካ የተደረጉት ሶስት ዝግጅቶች በሙሉ በደቡብ አሜሪካኖቹ አሸናፊነት ነው የተጠናቀቁት። በዘንድሮ ውድድር እስካሁን በተካሄዱ ጨዋታዎች ወደ ቀጣዩ ባለ16 ዙር ካለፉት መካከል ከአውሮፓ 6 ከደቡብ አሜሪካ ደግሞ 5 ቡድኖች ይገኙበታል።

ከነዚህ የአውሮፓ ቡድኖች የማሸነፍ አቅም እንዳለው እያሳየ ያለው አዳዲስ እና ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ያጣመረው የኔዘርላንድ ቡድን ነው። ሌላው በወጣት ኮኮቦች የተገነባው የፈረንሳይ ቡድንም ጥሩ ተፎካካሪ እንደሚሆን ያሳየ ቢሆንም የልምድ ማነስ ችግር  እስከ ፍጻሜ ይደርሳሉ ተብሎ አይገመትም። አንዳንዶች ደካማ ተሳትፎ ይኖረዋል ብለው የገመቱት የኔዘርላንድ ቡድን ባልተጠበቀ ሁኔታ የቀድሞዋን ቻምፒዮን ስፔንን 5 ለ 1 አሸነፎ ጠንካራ መሆኑን ካስመሰከረ በኋላ አውስትራሊያንም በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፍ አረጋገጠ። በተመሳሳይ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን ካረጋገጠው የደቡብ አሜሪካው ጠንካራ ቡድን ቺሊ ጋር ባደረገው ግጥሚያ በጥንቃቄ በመጫወት 2 ለ 0 አሸንፎአል። በደቡብ አሜሪካ አገሮች እግር ኳስ ደረጃ በአምስተኛነት የተቀመጠችው ቺሊ በጣልያኑ ጁቬንቱስ የሚጫወተው ነገር ግን ከኔዘርላንድ ጋር በተደረገው ጨዋታ ያልተሰለፈው አርቱሮ ቪዳል እና በባርሴሎና የሚጫወተው አሌክሲስ ሳንቼዝን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ነው።

60ሺ ሰው በሚይዘው ስታዲየም ውስጥ በነበሩ ከ40ሺ የቺሊ ደጋፊዎች ፊት በተካሄደው ጨዋታ ሆላንድ የተጠና ጨዋታ በመጫወት ወሳኞቹን ጎሎች አስቆጥረው የመጀመሪያ የደቡብ አሜሪካ ፈተናቸውን አልፈዋል። በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃ ቺሊዎች ሲያጠቁ ኔዘርላንድ በመከላከል ካለፉ በኋላ ለቀጣዮቹ 50 ደቂቃዎች ጎል አካባቢ ቦታ ባለመስጠት ጨዋታው መሃል ላይ የቀረበት አይን የማይስብ ሆኖ ነበር። ጨዋታው እንደፈለጉት የሄደላቸው ኔዘርላንዶች የተዳከመውን የቺሊ ቡድን ፍጥነት ባለው ጨዋታ ለማሸነፍ እንዲረዷቸው ሁለት ፈጣን ተጫዋቾችን በ70ኛ እና በ75ኛ ደቂቃ ላይ ቀይረው ባስገቡ በደቂቃዎች ውስጥ የመጀመሪያ ጎላቸውን በአንዱ ተቀያሪ አስቆጥረዋል። ወደ ጨዋታው መጨረሻ ሌላኛው ተቀያሪ ሁለተኛውን በማከል አሸናፊነታቸውን አረጋግጠው ጨዋታውን ፈጽመዋል። ከከባድ ተጋጣሚ ጋር በሚደረግ ጨዋታ ላይ መጀመሪያ መከላከል በኋላ ጨዋታውን ቀዝቀዝ አድርጎ ተጋጣሚን ማየት በስተመጨረሻ አጥቅቶ ማሸነፍ ለዋንጫ የሚሄድ ቡድን መለያዎች ናቸው። ኔዘርላንዶች ለስፔን ያዘጋጁትም መድሃኒት ተመሳሳይ ነበር። በዚሁ ከቀጠሉ በሊዮኔል ሜሲ የምትመራውን ሌላኛዋ የደቡብ አሜሪካ ሃያል አርጀንቲና ሁለተኛ ፈተናቸው ልትሆን ትችላለች።

ጥሩነሽ ዲባባ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን በሶስተኛነት አጠናቀቀች

ጥሩነሽ ዲባባ

ጥሩነሽ ዲባባ

ዛሬ በተካሄደው ታዋቂው የለንደን ማራቶን ላይ የተሳተፈችው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ 2 ሰአት ከ20 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ በመግባት የመጀምሪያ የማራቶን ውድድሯን በሶስተኛነት አጠናቃለች። ከባድ ከሚባሉ የማራቶን ውድድሮች አንዱ በሆነው በዚህ ማራቶን ውድድር ኢድና ኪፕላጋት እና ፍሎረንስ ኪፕላጋት የተባሉ ኬንያውያን ከጥሩነሽ በ14 እና በ11 ሰከንድ ቀድመው በመግባት አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው አጠናቀዋል። እስካሁን በአብዛኛው በ5ሺ እና 10ሺ ውድድሮች ላይ ብቻ ተወዳዳሪ የነበረችው ጥሩነሽ ከውድድሩ በኋላ እንደ መጀመሪያ ማራቶንነቱ በውጤቷ ደስተኛ መሆኗን እና ወደፊት በሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ላይ እንደምትሳተፍ ለጋዜጠኞች ተናግራለች። ጥሩነሽን በመከተል ፈይሴ ታደሰ እና አበሩ ከበደ 4ኛ እና 5ኛ ሆነው ሲጨርሱ የለንደን ኦሎምፒክ የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ቲኪ ገላና ውድድሩን በ9ኛነት አጠናቃለች።

በወንዶቹ ውድድርም የመጀመሪያ ማራቶኑን የሮጠው በትውልድ ሶማሊያዊ በዜግነት እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ውድድሩን በ8ኛነት ሲያጠናቅቅ በዚህ ውድድር ጸጋዬ ከበደ፣ አየለ አብሽሮ እና ጸጋዬ መኮንን ከ3ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ጨርሰዋል። ሌላው ኢትዮጲያዊ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ 9ኛ እና ኤርትራዊው ሳሙኤል ፀጋዬ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ማራቶኑን አጠናቀዋል።

የእግር መረብኳስ

የተለያዩ የመጠሪያ ስሞች ያሉት የእግር መረብኳስ ተብሎ የሚታወቀው ስፖርት ሶስት ሶስት ተጫዋቾች ያሏቸው ቡድኖች 1.5 ሜትር ከፍታ ላይ በተዘረጋ መረብ ተለያይተው በእግራቸው ብቻ የመረብ ኳስ የሚጫወቱበት ውድድር ነው። የተለየ መገለባበጥ ችሎታ የሚጠቀው ስፖርት በተለይ በምስራቅ እስያ በጣም ተወዳጅ ስፖርት ነው።

30ኛው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጲያውያን ስፖርት ፌስቲቫል ተጠናቀቀ

30ኛ አመቱን ያከበረው እና በሜሪላንድ ዩንቨርስቲ ስታድየም የተዘጋጀው የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጲያውያን ስፖርት ፌስቲቫል ባሳለፍነው ቅዳሜ ፍጻሜ አገኘ። በመዝጊያው እለት በተደረ የዋንጫ ጨዋታ ቨርጂኒያ ቦስተንን 4 ለ 2 በማሸነፍ የዘንድሮ ሻምፒዮን ሆኗል። ኢትዮጲያውያን ሴቶችን ማወደስ እንደ መርህ ይዞ በተዘጋጀው የ30ኛ አመት ውድድር መዝጊያ ላይ ዝነኛዋ አርቲስት መሰረት መብራቴ ለአሸናፊዎች ሽልማት አበርክታለች።

የፌስቲቫሉ ማጠናቀቂያ የሙዚቃ ምሽት ላይ ነጻነት መለሰ፣ ጃ ሉድ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ብርሃኑ ተዘራ፣ ሚካኤል በላይነህ እና ቴዲ አፍሮ ታዳሚዎችን ሲያዝናኑ አምሽተዋል።

This slideshow requires JavaScript.

30ኛው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጲያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ESFNA በድምቀት እየተካሄደ ነው

በሜሪላንድ የተበዘጋጀው እና 30ኛ አመቱን ያስቆጠረው የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌስቲቫል ESFNA ባለፈው እሁድ በደማቅ ፕሮግራም ተከፍቶ ታዳሚዎችን እያዝናና የቆየ ሲሆን በነገው እለት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ለውድድሩ በአሜሪካ እና ካናዳ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጲያውያን የተሰባሰቡ ሲሆን ከእግር ኳሱ ውድድር በተጨማሪ በርካታ ሙዚቀኞች በየምሽቱ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ኢትይጲያውያንን እያዝናኑ ይገኛል። ሃይሌ ሩትስ፣ አስቴር አወቀ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ሙኒት፣ ጃኖ ባንድ፣ ጃ ሉድ፣ መሃሙድ አህመድ እና ቴዲ አፍሮ ዝግጅቶቻቸውን ከውድድሩ ጋር አስታከው ለማቅረብ በከተማው ይገኛሉ።

በዝግጅቱ የተነሱ የተወሰኑ ፎቶዎችን ይመልከቱ

This slideshow requires JavaScript.