ናይጄሪያ እ.ኤ.አ በ2030 ጠፈርተኛ ወደ ህዋ ለመላክ አቅዳለች

ናይጄሪያ ጠፈርተኛ

የናይጄሪያው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዶ/ር ኦቦናያ ኦኑ በዋና ከተማ አቡጃ እቅዱን ይፋ ሲያደርጉ እንደተናገሩት የጠፈር ምርምር ስራዎች ለሃገራቸው በጣም ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል። የናይጄሪያው የጠፈር ማዕከል ባለሙያዎች ወደ ቻይና በማቅናት እቅዱን ለማሳካት ስለሚያስፈለጉ ዝግጅቶች መወያየት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

የሃገሪቱ ብሄራዊ የጠፈር ምርምር እና ልማት ባለስልጣን ባለፉት 15 አመታት 5 ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር አምጥቆ ከነዚህ ውስጥ ሶስቱ አሁንም አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ባለስልጣኑ ከ300 በላይ ባለሙያዎችን ይዞ እቅዱን ለማሳካት እየሰራ ሲሆን ጠፈርተኛ ከመላኩ በተጨማሪ የሃገሪቱን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ደረጃንም አብሮ ለማሳገድ ታስቦአል። የባለስልጣኑ የግንኙነት ባለሙያ እቅዱ ከተሳካ ለናይጄሪያ ብሎም ለአፍሪካ ትልቅ ኩራት እንደሚሆን እና የአፍሪካ አገራት ጠፈር ምርምር ላይ እንዲሳተፉ እንደሚያነቃቃ ተናግረዋል።

ኢትዮጲያም ከ11 አመት በፊት በጥቂት ባለሙያዎች እና በጎ ፍቃደኞች የተቋቋመው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበርም በዘርፉ በርካታ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ሲይገኛል። ከነዚህም መካከል ማህበሩ በእንጦጦ ተራራ ላይ ያስተከለው የህዋ መቃኛ ቴሌስኮፕ እና በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ባለሙያዎችን ለማስተማር እያደረገ ያለው ጥረት ይጠቀሳሉ።[CNN]

Advertisements

ግዙፉ የመኪና አምራች ቢ ኤም ደብሊዩ ከመቶ አመት በኋላ አገልግሎት ላይ ይውላል ያለውን መኪና አስተዋወቀ

ቪዥን ኔክስት 100

የተመሰረተበትን 100ኛ አመት እያከበረ ያለው ቢ ኤም ደብሊዩ እዮቤልዩውን ምክንያት በማድረግ በመጪው 22ኛ ክፍለዘመን መንገዶቻችን ላይ የሚታይ የተባለ የመኪና ሞዴል ዛሬ ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ በሰሙ ለሚያመርታቸው አራት የመኪና አይነቶች በሙሉ ከ100 አመት በኋላ የሚደርሱበትን ደረጃ በየተራ የሚያስተዋውቅ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው እና ቪዥን ኔክስት 100 የተሰኘው መኪና ዛሬ ለህዝብ ይፋ ሆኗል።

መኪናው ለየት ያለ የመሪ ቅርጽ ያለው ሲሆን እራሱን እየተቆጣጠረ ካለ ሹፌር እገዛ መንዳት የሚያስችል ብቃትም ይዟል። መኪናው የተዋወቀበትን እና የያዛቸውን ቴክኖሎጂዎች ከስር ካሉት ቪዲዮዎች ይመልከቱ።

በካቶሊኩ ጳጳስ የኢንተርኔት ጻዲቅ የተባሉት የሲቪያው ቅዱስ ኢዚዶር

የሲቪያው ኢዚዶር

የሲቪያው ኢዚዶር

እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ የነበሩት ጆን ፖል ትውልዳቸው በስፔኗ ሲቪያ ከተማ የሆነው እና እ.ኤ.አ በ676 ዓ.ም. የሞቱትን ኢዚዶርን የኢንተኔት የበላይ ጻዲቅ በማለት የቅድስና ማዕረግ ሰጥተዋቸዋል።

ኢዚዶር ኢንተርኔት ከመፈጠሩ ከ1ሺ 300 አመት በፊት ቢሞቱም ማዕረጉን ያስገኘላቸው ሰውየው በአለም ላይ ያለ ዕውቀት በሙሉ መመዝገብ አለበት ብለው በመወሰን መጽሃፎችን መጻፍ በመጀመራቸው ነው። ኢዚዶር የሰው ልጅ አለም ላይ ለመኖር የሚያስፈልገውን ማንኛውም እውቀት ማንንም ሳይጠይቅ በራሱ ማግኘት እንዳለበት በማመን የጀመሩት መጽሃፍ ከላቲን ፊደል አጻጻፍ ጀምሮ እስከ ሰውነት ክፍሎች፣ የተለያዩ የልብስ ስያሜዎች፣ የምግብ አይነቶች እና ሌሎችም በርካታ መረጃዎች መመዝገብ ችለው ነበር። በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት ለብዙዎች የመረጃ ምንጭ እንደሆነው ሁሉ በወቅቱ እውቀትን የሚፈልግ ሰው መረጃዎችን ለማግኘት ኢዚዶር ካዘጋጃቸው 20 መጽሃፎች ጎራ ማለት ይችል ነበር።

ኢዚዶር ቅድስናው ከካቶሊኩ ጳጳስ ቢሰጣቸውም የቫቲካኑ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማዕረጉን በይፋ አላረጋገጠውም። በዚህ የተነሳ አንዳንድ ካቶሊኮች የኢዚዶርን የቅድስና ማዕረግ አይቀበሉትም። [The Telegraph]

ከሰውነታችን በሚመነጭ ሃይል ተንቀሳቃሽ ስልካችንን ባትሪ ሙሉ ቻርጅ ለማድረግ ምን ያህል ግዜ ይወስዳል?

አአምሮ ኤሌትሪክ

የሰው ልጅ ኤሌትሪክ ሃይል ያመነጫል? አዎ!

የአእምሮአችን እና የነርቮች አሰራር፣ በህይወት የሚያቆየን የልብ ምት እና ስራ የሚያሰራን የጡንቻዎቻችን እንቅስቃሴ በሙሉ መሰረታቸው በሰውነት ውስጥ የሚመነጭ የኤሌትሪክ ሃይል ነው። የዚህ ሃይል ዋንኛ ምንጭ ደግሞ ከምንበላው ምግብ እና ከምንጠጣው ፈሳሽ ነገር የምናገኘው  የኬሚካል ንጥረነገር ነው።

በሰውነታችን የተለያዩ ቦታዎች ከሚመረተው የኤሌትሪክ ሃይል ውስጥ በደንብ ጥናት የተደረገበት አአምሮ ውስጥ ያለው ሲሆን ይሄም በአማካይ 0.085 ዋት ይሆናል። ይህ አነስተኛ የሃይል ምንጭ ቢሆንም በየቀኑ ከምንጠቀምበት ስልክ ጋር ማገናኘት ቢቻል ባትሪውን ቻርጅ ማድረግ ይችላል።

ለምሳሌ ገበያ ላይ ከቀረበ ሁለት አመት ገደማ የሆነው ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ 5 ባትሪ 10.78 ዋት-ሰዓት አቅም ሲኖረው ይህንን ባትሪ ከአአምሮአችን በሚመነጭ ኤሌክትሪክ ቻርጅ ለማድረግ

10.78/0.085 = 126.8 ሰዓት ወይም 5ቀን ከግማሽ ይፈጃል ማለት ነው። [gizmodo]

የኒውዮርክን የ500 ዓመት ገጽታ በሊፍት ውስጥ

በአሜሪካኗ ኒውዮርክ ከተማ እንደ አዲስ እየተገነባ ያለው የአለም የንግድ ማዕከል ህንጻ ውስጥ የተገጠመው አዲስ ሊፍት ከተማዋ ከ1500ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2015 ያላትን ገጽታ ማየት ይቻላል። ከህንጻው መግቢያ ጀምሮ እስከ ወለል ቁጥር 102 ድረስ በሚያደርገው ጉዞ ላይ አዲስ የመመልከቻ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሊፍት የከተማዋን ለውጥ በሁሉም አቅጣጫ ማየት ይቻላል።

የጉግል ፍለጋዎች በ2014

የአለማችን ትልቁ የኢንተርኔት መረጃ መፈለጊያ ድርጅት ጉግል ባወጣው መረጃ መሰረት በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2014 ዓ.ም ብዙ በመፈለግ በዚህ አመት ያረፈው ኮሜዲያኑ ሮቢን ዊሊያምስ፣ በብራዚል የተካሄደው 20ኛው የአለም ዋንጫ እና ምዕራብ አፍሪካ ብዙዎችን ለሞት እየዳረገ ያለው አደገኛው የኢቦላ በሽታ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

ከማሌዥያ ዋና ከተማ ኳላላምፑር ተነስቶ ወደ ቤይዢንግ በረራ ጀምሮ ድንገት ግንኙነት አቋርጦ የገባበት ያልታወቀው ኤም ኤች 370 የተሰኘው የማሌዢያ አየር መንገድ አውሮፕላን እና የአአምሮ ነርቭ ህመም ተጠቂዎች እንክብካቤ እና ህክምና ገንዘብ ለማሰባበሰብ በማህበራዊ ሚዲያ እይተሰራጨው የኤ ኤል ኤስ ቻሌንጅ አራተኛ እና አምስተኛ ሆነዋል። [Google]

በራሪ ብስክሌቶች

ለገበያ ይቀርባል ተብሎ የታሰበው በራሪ ብስክሌት ይህንን ይመስላል

ለገበያ ይቀርባል ተብሎ የታሰበው በራሪ ብስክሌት ይህንን ይመስላል

የሰው ልጅ የመጓጓዣ ችግሮችን ለማቃለል የሚረዱ ባለሁለት መዘውር መጓጓዣዎችን የመጠቀም ሃሳብ የመነጨው ከሁለት መቶ አመታት በፊት አካባቢ ነበር። አሰራሩ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ የመጣው ባለሁለት መዘውር መጓጓዣ አሁን የምናውቀውን የብስክሌት ቅርጽ ይዞ በስፋት ጥቅም ላይ ከዋለ ደግሞ ከመቶ አመታት በላይ ሆኖታል። በሰው ሃይል የሚጓዙትን ብስክሌቶች ለፈጣን መጓጓዣነት ብቁ ባለመሆናቸው በሞተር እንዲታገዙ የማድረጉ ሂደትም ከመቶ አመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ሞተር ብስክሌት ሰፊ ተቀባይነት እና ተጠቃሚ ካገኘ ወደ ስልሳ አመታት ገደማ ይሆነዋል። የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመፍጠር የሚደረገው ጉዞ በብስክሌቶችም ላይ የቀጠለ ሲሆን የወደፊቱ አቅጣጫው ወደ በራሪ ብስክሌቶች ዞሯል።

አስሸጋሪ መልክዓ ምድር ያለበት አካባቢ አገልግሎት ለመስጠት፣ በአደጋ ግዜ በቀላሉ ተጎጂዎች ጋር ለመድረስ፣ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ላይ ለመንቀሳቀስ እና ለመሳሰሉ ጥቅሞች ይውላል ተብሎ የታሰበውን ይህን በራሪ ብስክሌት እውን ለማድረግ ብዙ መሃንዲሶች እየለፉ ይገኛል። ስታር ዋርስ በተሰኘ ሳይንሳዊ የሆሊውድ ፊልም ላይ ሃሳቡ ከታየ በኋላ ነበር የበራሪ ብስክሌቶች ጉዳይ ብዙ ተቀባይነት ያገኘው። በአንድ ሰው የሚነዱት እነዚህ በራሪ ብስክሌቶች ከመሬት እስከ 5 ሜትር ከፍታ ላይ የሚበሩ ሲሆን ሁለት የሚሽከረከሩ አየር መቅዘፊያዎች (ፕሮፔለሮች) ይኖሩታል። የተለያዩ ድርጅቶች ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ፉክክር ላይ የሚገኙ ሲሆን በመጪዎቹ ሁለት እና ሶስት አመታት ለተጠቀሚ ይቀርባሉ የሚል ግምት አለ።

ስታር ዋርስ ሳይንሳዊ ፊልም ላይ የተዋወቀው በራሪ ብስክሌት

ስታር ዋርስ ሳይንሳዊ ፊልም ላይ የተዋወቀው በራሪ ብስክሌት

ሲ ኤን ኤን በቅርቡ በራሪ ብስክሌቶችን ከሚሰራ መሃንዲስ ጋር ያደረገው ቆይታ ከስር ይመልከቱ። [CNN]

ነጻ የኮምፒውተር ጸረ-ቫይረስ ፕሮግራሞች

ጸረ-ቫይረስ ፕሮግራሞች

በኮምፒውተር ላይ ያለን መረጃ ለመስረቅ፣ ለማበላሸት እና ለማጥፋት የሚሞክሩ በተለምዶ ቫይረስ ተብለው የሚጠሩ ፕሮግራሞችን ለማስወገድ እና ወደፊትም ኮምፒውተሩ ላይ እንዳይቀመጡ የሚከላከሉ ፕሮግራሞች በተለምዶ ጸረ-ቫይረስ የሚባሉ ፕሮግራሞች አሉ። እነዚህ የመከላከያ ፕሮግራሞች በክፍያ የሚገዙ ቢሆንም በነጻ ሊገኙ የሚችሉ በአገልግሎታቸውም ከባለ ክፍያዎቹ የማይተናነሱ ጸረ-ቫይረስ ፕሮግራሞች አሉ። በተለይ የዊንዶውስ የኮምፒውተር ስርዓት የሚጠቀሙ ኮምፒውተሮች በቫይረስ የሚጠቁ ሲሆን ከታች በተዘረዘሩት ፕሮግራሞች ተጠቅሞ ከስጋት ነጻ መሆን ይቻላል።

1. Bitdefender

2. avast!

3. Avira

4. AVG

5. FortiClient