ግዙፉ የመኪና አምራች ቢ ኤም ደብሊዩ ከመቶ አመት በኋላ አገልግሎት ላይ ይውላል ያለውን መኪና አስተዋወቀ

ቪዥን ኔክስት 100

የተመሰረተበትን 100ኛ አመት እያከበረ ያለው ቢ ኤም ደብሊዩ እዮቤልዩውን ምክንያት በማድረግ በመጪው 22ኛ ክፍለዘመን መንገዶቻችን ላይ የሚታይ የተባለ የመኪና ሞዴል ዛሬ ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ በሰሙ ለሚያመርታቸው አራት የመኪና አይነቶች በሙሉ ከ100 አመት በኋላ የሚደርሱበትን ደረጃ በየተራ የሚያስተዋውቅ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው እና ቪዥን ኔክስት 100 የተሰኘው መኪና ዛሬ ለህዝብ ይፋ ሆኗል።

መኪናው ለየት ያለ የመሪ ቅርጽ ያለው ሲሆን እራሱን እየተቆጣጠረ ካለ ሹፌር እገዛ መንዳት የሚያስችል ብቃትም ይዟል። መኪናው የተዋወቀበትን እና የያዛቸውን ቴክኖሎጂዎች ከስር ካሉት ቪዲዮዎች ይመልከቱ።

Advertisements

142 አገሮችን ያወዳደረ አንድ ጥናት ኢትዮጲያን 126ኛ ለኑሮ ምቹ አገር ደረጃ ሰጣት

ሌጋተም ኢንስቲትዩት

ሌጋተም ኢንስቲትዩት

መቀመጫውን በእንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን ያደረገው እና ብልጽግና በመላው አለም እንዲስፋፋ የሚሰራው መንግስታዊ ያልሆነው ሌጋተም ኢንስቲትዩት በየአመቱ የአለም አገራትን የብልጽግና ደረጃ በማወዳደር ይፋ ያደርጋል። ጥናቱ አገሮችን የሚያወዳድረው 8 የተለያዩ የመለኪያ መስፈርቶችን በመጠቀም ሲሆን እነሱም ፦ የኢኮኖሚ እድገት፣ ንግድ ስራ ለመጀመር ያሉ እድሎች፣ የመንግስት አስተዳደር፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ሰላም እና ደህንነት፣ የግል ነጻነት እና የማህበራዊ  ግንኙነቶች ጥንካሬ ናቸው። በነዚህ መስፈርቶች መሰረት ኢትዮጲያ በአለም ላይ ከተወዳደሩ 142 አገሮች 126ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 34 አገሮች ደግሞ የ23ኛ ደረጃን አግኝታለች።

ኖርዌይ ላለፉት 5 አመታት የያዘችውን የአንደኝነት ደረጃ ዘንድሮም በማስጠበቅ ለኑሮ ቀዳሚ ተመራጭ አገር ስትሆን ስዊዘርላንድ ሁለተኛ አንድ ደረጃ ያሻሻለችው ዴንማርክ ደግሞ ሶስተኛ ሆነዋል።
ከመጀመሪያዎቹ 10 ተመራጭ አገራት መካከል 7ቱ ከአውሮፓ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሶስት አገራት ኒውዚላንድ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ በቅደም ተከተል 4ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሌሎች አገሮችን ስናይ አሜሪካ 11ኛ፣ እንግሊዝ 15ኛ፣ ቻይና 52ኛ፣ ሩሲያ 58ኛ፣ ኬንያ 108ኛ ደረጃን አግኝተዋል።[LI]

በካቶሊኩ ጳጳስ የኢንተርኔት ጻዲቅ የተባሉት የሲቪያው ቅዱስ ኢዚዶር

የሲቪያው ኢዚዶር

የሲቪያው ኢዚዶር

እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ የነበሩት ጆን ፖል ትውልዳቸው በስፔኗ ሲቪያ ከተማ የሆነው እና እ.ኤ.አ በ676 ዓ.ም. የሞቱትን ኢዚዶርን የኢንተኔት የበላይ ጻዲቅ በማለት የቅድስና ማዕረግ ሰጥተዋቸዋል።

ኢዚዶር ኢንተርኔት ከመፈጠሩ ከ1ሺ 300 አመት በፊት ቢሞቱም ማዕረጉን ያስገኘላቸው ሰውየው በአለም ላይ ያለ ዕውቀት በሙሉ መመዝገብ አለበት ብለው በመወሰን መጽሃፎችን መጻፍ በመጀመራቸው ነው። ኢዚዶር የሰው ልጅ አለም ላይ ለመኖር የሚያስፈልገውን ማንኛውም እውቀት ማንንም ሳይጠይቅ በራሱ ማግኘት እንዳለበት በማመን የጀመሩት መጽሃፍ ከላቲን ፊደል አጻጻፍ ጀምሮ እስከ ሰውነት ክፍሎች፣ የተለያዩ የልብስ ስያሜዎች፣ የምግብ አይነቶች እና ሌሎችም በርካታ መረጃዎች መመዝገብ ችለው ነበር። በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት ለብዙዎች የመረጃ ምንጭ እንደሆነው ሁሉ በወቅቱ እውቀትን የሚፈልግ ሰው መረጃዎችን ለማግኘት ኢዚዶር ካዘጋጃቸው 20 መጽሃፎች ጎራ ማለት ይችል ነበር።

ኢዚዶር ቅድስናው ከካቶሊኩ ጳጳስ ቢሰጣቸውም የቫቲካኑ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማዕረጉን በይፋ አላረጋገጠውም። በዚህ የተነሳ አንዳንድ ካቶሊኮች የኢዚዶርን የቅድስና ማዕረግ አይቀበሉትም። [The Telegraph]

ከሰውነታችን በሚመነጭ ሃይል ተንቀሳቃሽ ስልካችንን ባትሪ ሙሉ ቻርጅ ለማድረግ ምን ያህል ግዜ ይወስዳል?

አአምሮ ኤሌትሪክ

የሰው ልጅ ኤሌትሪክ ሃይል ያመነጫል? አዎ!

የአእምሮአችን እና የነርቮች አሰራር፣ በህይወት የሚያቆየን የልብ ምት እና ስራ የሚያሰራን የጡንቻዎቻችን እንቅስቃሴ በሙሉ መሰረታቸው በሰውነት ውስጥ የሚመነጭ የኤሌትሪክ ሃይል ነው። የዚህ ሃይል ዋንኛ ምንጭ ደግሞ ከምንበላው ምግብ እና ከምንጠጣው ፈሳሽ ነገር የምናገኘው  የኬሚካል ንጥረነገር ነው።

በሰውነታችን የተለያዩ ቦታዎች ከሚመረተው የኤሌትሪክ ሃይል ውስጥ በደንብ ጥናት የተደረገበት አአምሮ ውስጥ ያለው ሲሆን ይሄም በአማካይ 0.085 ዋት ይሆናል። ይህ አነስተኛ የሃይል ምንጭ ቢሆንም በየቀኑ ከምንጠቀምበት ስልክ ጋር ማገናኘት ቢቻል ባትሪውን ቻርጅ ማድረግ ይችላል።

ለምሳሌ ገበያ ላይ ከቀረበ ሁለት አመት ገደማ የሆነው ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ 5 ባትሪ 10.78 ዋት-ሰዓት አቅም ሲኖረው ይህንን ባትሪ ከአአምሮአችን በሚመነጭ ኤሌክትሪክ ቻርጅ ለማድረግ

10.78/0.085 = 126.8 ሰዓት ወይም 5ቀን ከግማሽ ይፈጃል ማለት ነው። [gizmodo]

1.1 ቢልየን ዩሮ ወጥቶበት ስፔን ውስጥ የተሰራ አየር ማረፊያ በ10ሺ ዩሮ ለቻይና ድርጅት ተሸጠ

የሱዊዳድ ሬያል ሴንትራል አየር ማረፊያ

የሱዊዳድ ሬያል ሴንትራል አየር ማረፊያ

እ ኤ አ በ2008 ዓ.ም ተመርቆ ስራ የጀመረው የሱዊዳድ ሬያል ሴንትራል አየር ማረፊያ የሚገኘው ከስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ በስተደቡብ 235 ኪሜ ርቀት ላይ ሲሆን ምርቃቱን ተከትሎ የመጣው የአለም በተለይም የምራባውያን ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ኤርፖርቱን በ2012 እንዲዘጋ ምክንያት ሆኖት ነበር።

ኤርፖርቱን ለመሸጥ በወጣ ጨረታ ላይ የቻይናው ዛኒን ኢንተርናሽናል ብቸኛ ተጫራች ሆኖ 10ሺ ዩሮ በማቅረብ ጨረታውን አሸንፏል። የአየር ማረፊያው ባለቤት ቢያንስ 28ሚሊዮን ዩሮ እንዲሸጥ ፍላጎት እንዳለው ገልጾ እስከ መስከረም ያንን ዋጋ የሚያቀርብ ከጠፋ በ10ሺው ዋጋ ሽያጪ እንደሚፈጸም አስታውቋል።[Aljazeera]

ላይቤሪያ ከኢቦላ ነፃ ሆነች

ኢቦላ

ባለፈው አመት ምዕራብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ ከ4ሺ በላይ ዜጎቿን በሞት ያጣችው ላይቤሪያ በአሁኑ ወቅት ከበሽታው ነጻ መሆኗን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ። ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት እራሱ አስተማማኝ የህክምና አገልግሎት ያልነበራት ላይቤሪያ ወረርሽኙ ተጨማሪ ፈተና ሆኖባት ነበር። በንክኪ የሚተላለፈው ኢቦላ የህክምና ባለሙያዎችንም ለህልፈተ ህይወት መዳረጉ ደግሞ ለበሽተኞች አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ሌላ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሮ ነበር።

ከኢትዮጲያ፣ ቻይና፣ ኩባ እና ሌሎች አገራት የተላኩ የህክምና ባለሙያዎች በአለም አቀፉ የጤና ድርጅት አጋዥነት በሽታውን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት ላለፉት 42 ቀናት ምንም አዲስ የኢቦላ ተጠቂ ባለመመዝገቡ አገሪቷ ከኢቦላ ነጻ መሆኗ ታውጇል።

ከላይቤሪያ በተጨማሪ ወረርሽኙ የተከሰተባቸው ጊኒ እና ሴራሊዮንም የአዲስ ተጠቂዎች ቁጥር እየቀነሰ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ሁለቱም አገራት 9 አዳዲስ በሽተኞች ተመዝግበዋል።

የኒውዮርክን የ500 ዓመት ገጽታ በሊፍት ውስጥ

በአሜሪካኗ ኒውዮርክ ከተማ እንደ አዲስ እየተገነባ ያለው የአለም የንግድ ማዕከል ህንጻ ውስጥ የተገጠመው አዲስ ሊፍት ከተማዋ ከ1500ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2015 ያላትን ገጽታ ማየት ይቻላል። ከህንጻው መግቢያ ጀምሮ እስከ ወለል ቁጥር 102 ድረስ በሚያደርገው ጉዞ ላይ አዲስ የመመልከቻ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሊፍት የከተማዋን ለውጥ በሁሉም አቅጣጫ ማየት ይቻላል።